እንግሊዘኛ ፡ ሲባል ፡ ቀድመው ፡ በአይኔ ፡ ላይ ፡ የሚዞሩት ፡
ሞላ ፡ ያለ ፡ ጉንጭ ፡ ያላት ፡ ንግስት ፡ ቪክቶሪያ ፡ እና ፡ ንግስት ፡ ኤልሳቤት ፡ ናቸው፡፡ ሁለቱ ፡
ሊቃነ ፡ መናብርት ፡ በሀገራችን ፡ የሴቶች ፡ መብት ፡ ከወንዶች ፡ እኩል ፡ እዲከበር ፡ በቀጥታም ፡ ባይሆን ፡
በተዘዋዋሪ ጉልህ ፡ አስተዋእፆ ፡ አበርክተዋል፡፡
ለሰው ልጅ ተግባራዊ ክዋኔ የሐሳብ መነሻው አእምሮ ነውና ከዘመነ
መሳፍንት ወዲህ ገዢ የነበሩት የሀገራችን መሪዎች ትብብር ባስፈለጋቸው ጊዜ “ለከበሩት ንግስት…” እያሉ ለታላቋ
ብሪታንያ የወቅቱ ሴት ገዢዎች የመማፀኛ ደብዳቤ ሲፅፉ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሴቶች ከወንዶች እኩል አለመከበራቸውን
አስተዋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የሴቶች መብት መከበር እንዳለበት በነገስታቱ ልቦና ዳግም ተጠነሰሰ፡፡
የእህቶች ጉዳይ በንግስት ሳባ ታላቅነት ሽቅብ ወጥቶ በዮዲት ጉዲት
ክፉነት የተነሳ ቁልቁል ወርዷል፡፡ በዮዲት ጉዲት የተበሳጩት ባሎች ከዛን ጊዜ ጀምሮ በእርሷ እልህ ሚስቶቻቸውን
መደብደብ ጀመሩ፡፡ በኋላም እድሜ ለታላቋ ብሪታንያ ህዝብ አሳዳሪዎች ይሁንና ለእነርሱ ይፃፍ በነበረው ደብዳቤ
ምክንያት በኢትዮጰያ ነገስታት ልብ ዘንድ የሴቶች ጉዳይ ከተቀበረበት ተነስቶ አቧራው ሲወለወል፤ ቆየት ብሎ ደግሞ
በጣይቱ የተነሳ አንፀባረቀ!
እንዲሁ አማርኛ ሲባልም ውል የሚልብኝ ስነ-ስርአት ነው፡፡ ምንአልባት እንግሊዘኛ ከማወቄ በፊት ቁንጥጫ ስላጠቃኝ ይሆናል፡፡
ሳልቆነጠጥ ሰባተኛ ክፍል ደርሼ ቢሆንና ቀድሜ እንግሊዘኛ ባውቅ
“ዋ! ብቻ… እንዳልቆነጥጥህ!” ብለው ሲያስፈራሩኝ፤ ንግግራቸው ‘ትራጄዲ’ ሳይሆን ‘ኮሜዲ’ በሆነልኝ ነበር፡፡
ተቆንጥጠው ያላደጉ ልጆች ቁንጥጫ ማለት “እጅን ብብት ስር አስገብቶ መኮርር” ይመስላቸዋል መሰለኝ ሲያስፈራሯቸው
በመደንገጥ ፈንታ ይስቃሉ፡፡ እኔስ ቁንጥጫ ሲባል “የጭን መገሽለጥ” ትዝ እያለኝ እስከአሁን እንባዬ ነው
የሚቀድመው፡፡
የስነ-ስርአት ትርጓሜ በየትውልዱ ይለያያል፡፡ ጨዋታውን ቀያሪ
ስድስተኛው የስሜት ህዋስ ነው፤ ለጊዜው ቆሌ ብዬዋለው፡፡ ይሄ ቆሌ ‘ሚባል ልክ እንደ አማርኛ እንዳደረጉት
ይደረጋል፤ እንዳበጁትም ይበጃል፡፡ አንዱ ዘመን የሚደግፈውን ስነ-ስርአት ሌላኛው ዘመን ይነቅፈዋል፡፡ “ለምን?”
ሲባል “ዝም ብሎ”፤ ቆሌው ስላልወደደለት ብቻ! የፈለገውን ያከብዳል፣ ያልፈለገውን ያቀላል ፡፡ ያለፈውን አምጥተው
“ልጫን!” ቢሉ፤ ያልዎት ቀሪ እድሜ አነስተኛ ነውና ሰሚ አያገኙም፡፡
ድሮ ድሮ ከደጅ የሚመጣ ሰው ወደ ቤት ሲገባ ቅድሚያ በር ያንኳኳ
ነበር፡፡ የአሁኑ ትውልድ ሁሉን ነገር በየመንገዱ ስለሚጨርስና በር ተዘግቶ ምን ምን እንደሚሰራ ስለማያውቅ፤
አያንኳኳም፡፡ አብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪም አራት የኮንዶሚኒየም ፎቆች ደረጃን እየወጣ ከበሩ ስለሚደርስ አንኳክቶ
“ደህና ዋላችሁ?” የሚልበት ትንፋሽ አይኖረውም፡፡
ጠባብ ልብስ እና በከፊል ራቁት ሆኖ መሄድ ፋሽን ከሆነ
ቆየ፡፡ ሊወቅሱት ቃላት ከመዘዙ መልስ አያጣም፤ “ጠባብ እና ሰውነት የሚያሳይ ልብስ የምንለብሰው ሀገራችን ሰፊው
ግዛቷ ስለጠበበና የደን ሀብታችን ተመናምኖ መሬቱ ራቁቱን ስለቀረ ነው!” ይልዎታል፡፡ አብዮት መሆኑ ነው እኮ¡
ጠበሳውም የተሳለጠ ነው እንደበፊቱ አበሳ የለበትም፡፡
ከላይ በመግቢያዬ በእያንዳንዱ ፊደል መሀከል ሁለት ነጥብ ያደረግኩትኝ የድሮውን ስርአተ ነጥብ ለማመልከት ነው፡፡ የሁለት ስርአተ ነጥቡን አጠቃቀም የወደዳችሁት ብትኖሩ… አጥንታችሁን አስመርምሩት!
ነጠላ ሰረዝ፣ ድርብ ሰረዝ፣ ያንቀፅ መለያ፣ ትምህርተ ጥያቄ፣
እጥር (የዛሬው ቅንፍ)፣ ይዘት፣ ፍጀታ፣ እስከ፣ ትምህርተ አንክሮ፣ ትምህርተ ስላቅ፣ ትምህርተ ጥያቄ፣ መከልል እና
ነጠብጣብ የተባሉትን የአማርኛ ስርአተ ነጥቦች ባንተዋቸውም ሁለት ነጥብን ግን ወዲያ ካልነው ቆየን፡፡ ደግ! ምንም
ቅሬታ የለኝም፡፡ እንዳንረሳው ብቻ ማህደሩ ተዘግቶ ከታሪክ መዝገብ ቤት ይቀመጥ፡፡ በነጥቡ ፈንታ ክፍተት
መጠቀማችን ድካም ይቀንሳል፡፡
ሁለት ነጥብን ማስቀረት ስነ-ፅሁፋዊ ስርአት አልበኝነት ቢሆንም ወዝ ያለው ስርአት አልበኝነት ከስነ-ስርአት ይቆጠራል፡፡
በተጨማሪም ውበት ማጉላቱ ሸጋ ነው!
ወጣቶች ስትዘምኑ
…………………ሎሚና ትርንጎ ሞልቶ በሀገር …………………እንቧይ ያስሸትታል የደሃ ነገር >>>>> አይምሰል ዘመናዊነታችሁ! ውስጡ ባዶ የሆነ አብረቅራቂውን ሁሉ አታንጋጉ፡፡
ስትሰጥኑ’ም “እውር ሲቀናጣ ምርኩዙን ወርውሮ ብሬክ ይደንሳል!”
እንደተባለው አይነት አይሁንባችሁ! ሳያውቁ የቆረጡት አበባ የፈለጉት ቀን ይደርቃልና መቁረጥ የማይገባችሁን
አትቁረጡ፡፡ መሰረት ሳትለቁ ወዝ ባለው መልኩ ዘምኑ! ምርኩዝ አትጣሉ!
ባለፈው ሰሞን ለእማማ ኢትዮጵያ ከመንግስተ ሰማይ ስልክ ተደውሎላት … “ምነው መልክሽ ከሰማይ አልታይ አለኝ?” ተብላ ስትጠየቅ “አረጋዊ ስለሞተ ከደጃችን ድንኳን ተተክሏል!” አለች፡፡
“እባካችሁን በያላችሁበት የከለላትን ድንኳን ንቀሉ! የእናት ሀገራችን መልክም ጥርት ብሎ ከሰማይ ይታይ!”

Post a Comment